Thursday, 31 July 2014

ግጥሞች

መኖር መርጫለሁ አምላኬ አንዲት ነገር እለምንሃለሁ፣ እርሷንም እንዳገኝ እጅጉን እሻለሁ፣ በቤትህ ወድቄ መኖር መርጫለሁ፡፡ ሞትን ላለመሞት ሞትን ላለመሞት፣ ለመኖር በሕይወት፣ ንስሓን መድኃኒት፣ እንግዛ ከካህናት፡፡ እኔን ረሳሁት የሰዎችን ኃጢአት ሳነሣና ስጥል፣ የዓይናቸውን ጉድፍ ለማውጣት ስታገል፣ የእኔን እያሳረርኩ የሰውን ሳማስል፣ ዘመኔን ጨረስኩት በከንቱ ስዋልል፡፡ ሰውን በኃጢአቱ ሁልጊዜም ሳስታውስ፣ እኔን ረሳሁት ይገርማል የእኔ ሰው መሆንስ፡፡ ዕለቱ ዛሬ ነው ዕለቱ ዛሬ ነው የንስሓ መግቢያ፣ ከኃጢአት ከበደል እድፍ መታጠቢያ፡፡ ኃጢአትና በደል ሁልጊዜ ስንሠራ፣ ሲከመር ሲቆለል ልክ እንደተራራ፣ ንስሓ ሳንገባ ከኃጢአት ሳንጸዳ፣ የምንኖር ከሆነ አቤት የእኛ ዕዳ፡፡ ዕለቱ ዛሬ ነው ነገ ሌላ ቀን ነው፣ ንስሓ ለመግባት አሁን መወሰን ነው፡፡ ከንቱነቴ ገንዘብ ቢበዛልኝ ቢሞላ ጎተራው፣ ፎቁን በፎቁ ላይ ደርቤ ብሠራው፣ በልቼ ጠጥቼ ጠግቤ ረክቼ፣ በሚያምር መኝታ ባድር በሰላም ተኝቼ፣ ነፍሴን ካልጠቀምኳት ካልተንከባከብኳት፣ ከንቱነቴ ይህ ነው የዘላለም ጉዳት፡፡ ወቀሳ አንተ እያልኩ ብወቅስህ፣ ወንድሜ ሆይ ቅር አይበልህ፣ አንተ የምለው፣ አንተን፣ እኔን፣ እርሷን፣ እኛን በጋራ ነው፡፡ ተነሡ ለጸሎት በሰላም አውለን በቸር አሳድረን፣ ብለን እንድንኖር ፈጣሪን ለምነን፣ ተነሡ ለጸሎት እንጸልይ ተነሥተን፣ ስንፍና ልቡና ድካምን አርቀን፡፡ ያለገንዘብ ገዝተን አንዴ ከበላነው የማያስርበውን፣ አንዴም ከጠጣነው የማያስጠማውን፣ ነጽተን ተዘጋጅተን በትሕትና ሆነን፣ የዘላለም ሕይወት የምንወርስበትን፣ ያለገንዘብ ገዝተን እንብላ ሥጋውን፣ እንጠጣ ደሙን፡፡ አናንቀላፋ እንዳንጥለው የያዝነውን ወርቅ አልማዝ ዕንቍውን፣ አናንቀላፋ እንቅልፍን፣ እንደገፍ እምነት ምርኩዝን፡፡ መስታወቴ ኃጢአቴን የሚያሳየኝ፣ ከንቱነቴን የሚነግረኝ፣ መጽሐፍ ቅዱስ መስታወቴ፣ የተሰጠ ለእኔነቴ፡፡ ለካስ ራሴ ነኝ ኃጢአትን ገዝቼ ሕሙማን ልጠይቅ፣ በሲዖል ያሉትን በጨለማ ድቅድቅ፣ የምሄድበትን ቀን እንኳ ሳላውቀው፤ ዛሬ ነገ እያልሁ ሞቴን ስጠብቀው፣ ቀማኝ ኃጢአቴን ንስሓ ኃይለኛው፣ እንደጢስ አትንኖ መድረሻም አሳጣው፣ ለካስ ራሴ ነኝ ዋና ሕመምተኛው፡፡ ራበኝ ኃጢአትን አብዝቼ በላሁኝ እጅግም ጠገብኩኝ፣ በዓለምም ባሕር ውስጥ ገብቼ ዋኜሁኝ፣ አሁንስ በቃኝ መረረኝ ከልክም በላይ ሰለቼኝ፣ የጽድቅ እንጀራ ራበኝ፡፡ እጄን ታጥቤ የምበላው በንጽሕናም የምጎርሰው፣ የዘላለም ሕይወትን እንዳገኝ የሚያደርገው፣ እውነተኛ መብል ሥጋ ወደሙ ነው፡፡ እናቴ ናት ከዓለም አሽክላ ወጥመድ አመለጥኩ፣ በድንግል ማርያም እየተደገፍኩ፣ ድንግል ማርያም እናቴ ናት ለዘላለም፣ ድኜባታለሁ ከኃጢአት ዝናም፡፡ ይኼው እምላለሁ በባቢሎን ወንዞች በዚያ ተቀምጠን፣ ጽዮንን ስናስብ እጅግ አለቀስን፣ መሰንቆዎችንም ከዛፍ ላይ ሰቀልን፡፡ የማረኩኝ በዚያ ዝማሬን ፈልገው፣ የጽዮን ዝማሬን ፈለጉብኝ ተግተው፡፡ በኃይላቸው ብዛት ማርከው ቢያስፈራሩኝ፣ በባዕድ አገር ላይ አልዘምርም አልኩኝ፡፡ በስደት ብሆንም በግፍ በመከራ፣ ጽዮንን ላስባት አለብኝ አደራ፡፡ ኢየሩሳሌምን ላልረሳት ቃል ገባሁ፣ በሕያው አምላኬ ይኼው እምላለሁ፡፡ የሞት ሞት በበደል ከኖርን በኃጢአት፣ ለጽድቅ ካልሰጠናት ትኩረት፣ ንስሓን ጠልተን ከናቅናት፣ የኖርን አይምሰለን በሕይወት፣ ስለሆነብን የሞት ሞት፡፡ መስቀል አምላክ ዙፋኑ ያደረገህ በደሙ መፍሰስ የቀደሰህ፣ ሥጋውን ባንተ ቆርሶ ነፍሳትን ያዳነብህ፣ መስቀል ቅዱስ መድኃኒት መጽናኛ ነህ፣ ኃይላችን ትምክህታችን አንተ ነህ፣ የጠላት ማሳፈሪያ ጋሻችን ነህ፡፡ ማነህ አንተ መጾም ስትችል የምትበላ፣ መውደድ ስትችል የምትጠላ፣ መስማት ስትችል የደነቆርህ፣ መኖር ስትችል ሞት የመረጥህ፣ መጽደቅ ስትችል ወደ ኃጢአት፣ መስገድ ስትችል የማትሰግድ፣ መሄድ ስደትችል የማትሄድ፣ መቀደስ ስትችል የምታረክስ፣ የማታስብ ስለ ነፍስ፣ መስከር መዝፈን መደነስ፣ ብቻ የሆነ ሥራህ፣ አስተዋይ ልብ የሌለህ፣ በውኑ ኧረ አንተ ማነህ? ምነው ዛለ የቆመ የመሰለው እንዳይወድቅ፣ ሁሌም ይንቃ ይጠንቀቅ፣ የሸንበቆ ምርኩዝ ይዞ፣ አያስፈልግም የትም ጉዞ፣ ተኩላ ከበግ ጋር እየዋለ፣ መከላከያህ ምነው ዛለ? ቤተ ክርስቲያን ምነው ጠላት ቀስቱን ሰበቀብሽ፣ ለምን ጡትሽን ነከሱ ልጆችሽ፣ ምን አይነት ልጆች ተፈጠሩ፣ ታላቃቸውን የማይፈሩ የማያፍሩ፣ ቤተ ክርስቲያን እናቴ፣ የዘላለም ማረፊያ ቤቴ፣ እኔስ ጡትሽን አልነክስም፣ ወተትሽን እጠባለሁ ዛሬም ነገም፡፡ አንችን ምን ብሆን ላልክድሽ፣ ቃል ገባሁልሽ በፊትሽ፡፡ ጾም የነፍሴን ቁስል የምትፈውስ፣ መድኃኒት ናት ለእኔስ፣ ሥጋዬን ላክሳው በቅቤ ማጣት፣ ነፍሴ በጽድቅ እንድትገዛት፣ ያለ ጾም ጸሎት ላይወጣ ጋኔን፣ ሌሎች ቢጠሉሽ አልጠላም አንችን፡፡ ዮሐንስ ልሁን ከመስቀሉ ሥር የተገኘውን በመከራ ያልተለየውን፣ አምላክ እናቱን ያስረከበውን ምሥጢረ መለኮት የበዛለትን፣ በክርስቶስ ጭን ቁጭ ያለውን ፍትወተ ሥጋ የጠፋለትን፣ ሐዋርያውን ባለ ራዕዩን ዮሐንስ ልሁን፡፡ ጸሎት እንደ አንቺ ያለ መሣሪያ፣ ፈጣሪን ማናገሪያ፣ አባቶቼ የሠሩልኝ፣ ጸሎት ገንዘቤ ሁኝልኝ፣ ሰባት ጊዜ ላመስግን እግዚአብሔር አምላኬን፣ ድንግል ማርያም እናቴን ቅዱሳንን ሁሉ አባቶቼን፡፡ ዝምታን መረጥኩ ያንን የሚያቃጥል እሳት፣ የማይወሰን መለኮት፡፡ ዘመን ሊቆጠርለት የማይችል፣ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል፡፡ እግዚአብሔር ቃል ወልድ፣ ከሰማየ ሰማያት ሲወርድ፡፡ ድንግል ሥጋሽ ያልተቃጠለው፣ እመቤቴ ኧረ እንዴት ነው? እስኪ ንገሪኝ ለልጅሽ፣ በትሕትና ልጠይቅሽ፡፡ እንዴት ወለድሽው፣ የት አስቀመጥሽው፡፡ እሳት መታቀፍ እንዴት ተቻለሽ፣ ምን አይነት ወተት መገበው ጡትሽ፣ አንቺ እኮ ከሴት ማንም አይመስልሽ፡፡ ላመሰግንሽ ብፈልግም፣ አንደበቴ አንችን መግለጽ አይችልም፡፡ ዲዳ ነኝና ዝምታን መረጥኩ፣ እንድትፈችልኝ እየተማጸንኩ፡፡ ሥጋ ለበሰ ዲያብሎስ በእባብ ተሰውሮ፣ አዳምን ቢያወጣው ከገነት ጓሮ፡፡ ሥጋ ለበሰ አምላክ ክርስቶስ፣ ወደ ቀደመ ክብሩ ሊመልስ፡፡ አዳም በበደለ ኃጢአት በሠራ፣ አምላክ ተቀበለ ያንን መከራ፡፡ ምን ይከፈላል ለዚህ ውለታህ፣ ተመስገን ብቻ ነው የምንልህ፡፡ ወድሰኒ በይኝ ወድሰኒ በይኝ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም፣ ላመስግንሽ እናቴ ድንግል ማርያም፡፡ ምሥጋናሽን ትምህርትሽን አብዝተሽ፣ በልቤ ውስጥ ጨምረሽ፡፡ እንደ አሸዋ እንደ ከዋክብት፣ ስፍር ቁጥር የሌለው በብዛት፣ በመጠን እጅግ የበዛ ቁጥር የሌለው ድርሰት፣ እንድደርስ ስጭኝ ንጹሕ ትሑት አንደበት፡፡ የሚጥመውን እንደ ማር ሥምሽን እንድጠራ፣ ወድሰኒ በይኝ እኔን በቅዱስ ኤፍሬም ተራ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ነደ እሳት፣ ያደርክ በሐዋርያት፡፡ ምሥጢር ገላጭ መንፈስ ቅዱስ፣ እኛንም ባርክ አድርገን ቅዱስ፣ አጽናን አበርታን እንድንኖር በሕይወት፣ ቀድሰህ አንጽተህ አድርገን የገነት ባለቤት፡፡ ጣዖት እጅ እያለው የማይዳስስ፣ በእገሩ የማይሄድ ልፍስፍስ፡፡ ጆሮ ሳለው የማይሰማ ደንቆሮ፣ ጣዖት ይውደቅ ተሰባብሮ፣ ላይጠቅማችሁ ላይረባችሁ፣ ሰዎች አታምልኩት እባካችሁ፡፡ ስጠኝ ንጹህ ልቡና አምላኬ ሆይ አንዲት ነገር ልለምንህ፣ ፈጽምልኝ ይሁንና ቅዱስ ፈቃድህ፡፡ ልቤን ንጹህ የሚራራ አድርግልኝ፣ ቅዱስ መንፈስህንም በውስጤ አድስልኝ፡፡ አንተን ለማመስገን ሁልጊዜ የሚቀና፣ አምላኬ ሆይ ስጠኝ ንጹህ ልቡና፡፡ ዛሬ ፍረድና እሳቱ ማይጠፋ ትሉ ማያንቀላፋ፡፡ የኩነኔ ቦታ ድቅድቁን ጨለማ፣ አምላኬ አታውርሰኝ ስትመጣ በግርማ፡፡ አታሳዬኝ እኔን እፈራለሁና፣ ገነትን አውርሰኝ ዛሬ ፍረድና፡፡ ዶሮ ሲጮኽ በልቤ እያመንኩ በአፌ ብክድህ፣ አላውቅህም ብልህ፡፡ እንደ ጴጥሮስ ደጋግሜ፣ በብርድ በሽታ ታምሜ፡፡ አንተ አምላኬ ተቀበለኝ፣ በንስሓ ተመለስኩኝ፣ እንደ ቀድሞው ልጅ አድርገኝ፣ ዶሮ ሲጮኽ እኔም ጮኽኩኝ፡፡ አንተን ተጠግቼ ሥጋህን ያልበላ ደምህን ያልጠጣ፣ የዘላለም ሕይወትን ከሆነ የሚያጣ፡፡ ሥጋህን በልቼ ደምህን ጠጥቼ፣ እኖራለሁ እኔስ አንተን ተጠግቼ፡፡ አውሎግሶን አቤቱ ግለጥልኝ፣ አቤቱ ክፈትልኝ፡፡ የተዘጋ አንደበቴን፣ ስለምንህ ብዬ አውሎግሶን፡፡ ባሕራንን የረዳኸው፣ ሞቱን ሕይወት ያደረከው፡፡ ሶስናን የጠበቅሃት፣ ከእደ ረበናት፣ አፎምያን ያጸናሃት፣ በተዋሕዶ እምነት፡፡ እኔንም ጠብቀኝ፣ ሌሊት ከቀን ጋሻ ሁነኝ፡፡ አውሎግሶን ብዬሃለሁ፣ ሚካኤል ሆይ አምንሃለሁ፡፡ ገብርኤል በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው፣ ወደ ድንግል የተላከው፡፡ ሦስቱን ሕጻናት፣ ያወጣቸው ከነደ እሳት፡፡ ቂርቆስና ኢየሉጣን፣ የፈቀደ ለማዳን፣ አቀዝቅዞ የፈላውን፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል፣ ዛሬም አውጣን ከኃጢአት ማዕበል፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን ወደ ቤተክርስቲያን እንሂድ ሲሉን፣ እንደ ንጉሡ ቅዱስ ዳዊት ደስ ይበለን፣ በረከት ረድኤት ፍቅር እንዲበዛልን፡፡ እንገስግስ ለጸሎት ለቁመት ማልደን፣ ወደ እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ፡፡ የአባቴ ቡሩክ ነህ ተርቤ አበላሃኝ ጠምቶኝ አጠጣሃኝ፣ በእንግድነት ተቀበልከኝ ታምሜ ጠየቅኸኝ፣ ታስሬ አስፈታሃኝ ታርዤ አለበስከኝ፡፡ ለፍርድ ቀን መጥተህ፣ በፊትህ አቁመህ፡፡ እንደዚህ ከሆነ እኔን የምትለኝ፣ እንድፈጽማቸው ዛሬ ኃይል ስጠኝ፡፡ እኒህን ፈጽሜ ከተገኘሁማ፣ አምላኬ ስትመጣ በሚያስፈራ ግርማ፡፡ ከቅዱሳንህ ጋር በቀኝህ አቁመህ፣ ዓለም ሳይፈጠር ካዘጋጀሁልህ፣ ከደስታ ቦታህ ሰማያዊ ርስትህ፣ ግባ ደስ ይበልህ የአባቴ ቡሩክ ነህ፣ አንተው ትለኛለህ፡፡ ቀጠሮ ንስሓ ለመግባት ስንቀጥር ቀጠሮ፣ ዛሬ ነገ ስንል ከድሮ ጀምሮ፡፡ ነገ ነገን ወልዶ ነገን እየተካ፣ ዘመን በዘመናት እየተተካካ፡፡ ቀኑ እየከነፈ በሞታችን ሊደርስ፣ የእኛኑ ቀጠሮ እኛው ስናፈርስ፡፡ ባልታወቀ ሰዓት ባልታሰበ ዕለት፣ ክፈቱልኝ ብሎ ሲያንኳኳብን ያ ሞት፡፡ ምን እንመልስ ይሆን አቤት የሰው ነገር፣ ቀጠሮ አንሰጠው ሞት እኛን አይቀጥር፡፡ ቀጠሮ ቀጠሮ ሁልጊዜ ቀጠሮ ከሆነ ቀጠሮ፣ ሊፈታ የማይችል ይሆናል ቋጠሮ፡፡

No comments:

Post a Comment