Thursday, 31 July 2014

እንመለስ

በዚያ ስቃይ ዓለም በድቅድቅ ጨለማ፣ በካራን የኖርነው በኃጢአት ከተማ፡፡ በስካር በዘፈን በሐሜት በዝሙት፣ በጭፈራ በዳንስ በክርክር በምዋርት፣ በመግደል በመስረቅ በመናፍቅነት፣ በጥል በአድመኝነት በቁጣ በቅንዓት፡፡ ምቀኛ በመሆን ጣዖትን በማምለክ፣ ለጠንቅዋይ ተገዝተን ፊቱ በመንበርከክ፣ ብዙ አሳልፈናል የጨለማን ታሪክ፡፡ ከአምላክ ተለይተው የሚኖሩት ሕይወት፣ ይመራናልና ወደ ዘላለም ሞት፣ እንመለስ ዛሬ በቁማችን ሳንሞት፡፡ ከበረከቱ ምንጭ ሁልጊዜ የሚያጠጣን፣ ፀሐይን የሚያወጣ ለኃጥአን ለጻድቃን፣ የላከልን ለኛ የቸርነት ክንዱን፣ እኛ ስንበድለው እርሱ የሚክሰን፣ እኛ ስንጠላው እርሱ የሚወደን፣ በጠፋንም ጊዜ እርሱ የፈለገን፣ ሞት መርጠን ስንወድቅ ሕይወትን የሰጠን፣ እግዚአብሔር በውኑ ምን አጎደለብን? ቀንም ለሥጋችን ሌትም ለሥጋችን፣ ጠዋት ለሆዳችን ማታም ለሆዳችን፣ ሥጋን ማድለብ ብቻ ለሆነ ሥራችን፣ ማሰብ ይገባናል ለአንዲቷም ነፍሳችን፡፡ ይህ ነው የሚጠቅመን የነፍስ በረከት፣ በፍቅር በደስታ በሰላም በትዕግሥት፣ በእምነት በቸርነት በሥራ በጎነት፣ የዋሃት በመሆን ራስን በመግዛት፣ መኖር ይገባናል ሳንርቅ ከአምላክ ቤት፡፡ ከእግዚአብሔር ርቀው ቢደክሙ ቢለፉ፣ ኪሳራ ብቻ ነው ኪሳራ ነው ትርፉ፡፤ ያለንን ባርክልን ብለን ብንለምነው፣ አምስቱን እንጀራ ለዓመት ነው ሚያደርገው፣ ሊያበረክትልን የታመነ አምላክ ነው፡፡ የሰማይ ወፎችን የሚመግብ አምላክ፣ የምድር አበቦችን ያስጌጣቸው አምላክ፡፡ በአምሳሉ በአርአያው የፈጠረ እኛን፣ እንዴት ነው የሚተወን እንዴት ነው የሚረሳን? ይልቅ እንመለስ ወደ አምላክ እግዚአብሔር፣ ይሻለናልና መኖር ተጣብቀን ከእርሱ ጋር፡፡ ሁሉንም አየነው አየነው ሁሉንም! የወፈረውንም የቀጠነውንም፣ ብዕል የበዛለትን ምን የሌለውንም፣ ንጉሠ ነገሥቱን የሚገዛውንም፣ ባለሥልጣኑንም ተገዥ ሕዝቡንም፡፡ አፈር ነው የበላው ከመቃብር በታች፣ ንብረቱን ሲያከማች፡፡ ታዲያ ምን ይረባል የዚህ አይነት ኑሮ፣ መሞታችን ላይቀር እንዲህ ዞሮ ዞሮ፡፡ ከአምላክ ጋር ለመኖር ዛሬው ወስነን፣ ከኃጢአት እንውጣ እንመለስ ይብቃን፣ በሰይጣን ባርነት የኖርነውን ትተን፣ ሰብረነው እንምጣ በንስሓ ታጥበን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀን፡፡ ሥጋውን እንብላ ደሙንም እንጠጣ፣ ለዘላለም ኑሮ ይህ ነው የሚያዋጣ፡፡

No comments:

Post a Comment